(ክንፉ አሰፋ)
አንድ የኢህአዴግ ካድሬ፣ ቤት ለመከራየት ወደ አንዲት ወይዘሮ መኖርያ ይሄዳል። ስፍራው እንደደረሰ ሌላ ተከራይም ከወይዘሮዋ ቤት ብቅ እንዳለ አስተዋለ። ሌላኛው ተከራይ ሰይጣን ነበር። ሁለቱ ተከራዮች ሰርቪስ ቤቱን ለመያዝ እንደ ጨረታ ብጤ ጀመሩ። ሰይጣኑ 400 ሲጠራ፣ ካድሬው ግን 500 ሊሰጥ ተስማማ። በመጨረሻ፣ ወይዘሮዋ ቤቱን ለሰይጣኑ በትንሽ ዋጋ ማከራየቱን መረጡ። የወይዘሮዋ ውሳኔ እንግዳ ነገር ነበር። ለሰይጣን፣ ለዚያውም በትንሽ ዋጋ ቤታቸውን ለመስጠት የወሰኑበትን ምክንያት ሲጠየቁ፤ “ሰይጣኑ አልወጣ እንኳን ቢል በጸበል ይለቃል። ካድሬው ገብቶ ቤቴን አልለቅም ቢለኝ ምን ላደርግ ነው?” ነበር ያሉት ወይዘሮዋ። ከፍ ባለ ገንዘብ ለኢህአዴጉ ሰርቪስ ቤታቸውን ቢያከራዩት ኖሮ ባጭር ጊዜ ዋናውን ቤታቸውን ለቀው የመውጣት ክፉ እድል ይገጥማቸው ነበር።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ባለፈው ሳምንት ዘ ሄግ ላይ ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲነግሩን ጣል ያደረጓት ቀልድ ናት። የዚህች ቀልድ የፖለቲካ እንድምታ ቀላል አይደለም። መልእክትዋ ሲጠቃለል የኢትዮጵያን ህዝብ እየለቀቀ መሆኑን ትነግረናለች። እየከፋ የመጣው የኑሮውና የፖለቲካ ሁኔታ የህዝቡን አእምሮ ብቻ አይደለም እየነካው ያለው። ህዝቡ እየተገፋ ሃገርሩን ለቆ እንዲሰደድ እየተገደደም ይገኛል። በተለይ ደግሞ ሃገሪቱ በድህነት ያስተማረቻቸው ምሁሮችዋንና ባለሞያዎችዋን እንደዋዛ እያጣች ከመጣች እነሆ ሁለት አስርተ-ዓመታት ተቆጠሩ።
እለተ ሰኞ የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም.።
የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት የጣለው በኢትዮጵያዊው ፓይለት ጉዳይ ላይ ነበር። እንደዚህ አይነት ክስተት ሲፈጸም አዲስ አይደለም። ግን ይኽኛው ልዩ ነው። ይዘቱ ለየት ይበል እንጂ በ1998 (እ.ኤ.አ.) ዩዋን ቢን በተባለ ቻይናዊ ፓይለት ከተፈጸመው ድርጊት ጋር ይመሳሰላል። የ30 አመቱ ወጣት የበረራ ቁጥር CA905 የሆነውን የቻይና አውሮፕላን በመያዝ የታይላንድን የአየር ጠረፍ ሰብሮ ገባ። የ27 አመት እድሜ ያላት ሚስቱን ይዞ ታይዋን ላይ ያረፈው ፓይለት ለዚያ አደገኛ ውሳኔ የሰጠው ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ነበር። የደረጃ እድገት፣ የደሞዝ ጭማሪ፣ የመሳሰሉ ከራስ ወዳድነት ያላለፉ ጥያቄዎች በማንሳት የፓይለቱ የራሱን ክብር ዝቅ አደረገው።