የኮንትራት ሰራተኞች ስቃይ፣ የእኛ ፍርሃትና የፖለቲከኞች ጭካኔ
እረፍት አደርግ ብየ ከማህበራዊ መገናኛ መድረኩ ገለል ባልኩባቸው እንደ ብርሃን ፍጥነት በሚወረወሩት ባለፉት ጥቂት ቀናት ከበርካታ ወዳጆቸ በርካታ መልዕክቶች ይደርሱኛል። ብዙው መልዕክት ደግሞ የሚያጠነጥነው በጅዳ እና በአካባቢው በተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች አሰቃቂ ስቃይ ላይ ያተኮራል … ለነገሩ የአብዛኞቹ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆኑ ከመልዕክቶች ጋር የሚላኩልኝ መረጃዎች እረፍት የሚነሱ ናቸው! …
አዎ ተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር በመረጃነት የታጨቀባቸውን የመልዕክት መረጃ ጭብጦች እውነታ ለማረጋገጥ ወደ ጅዳ ቆንስል አመራሁ … መኪናየን አቁሜ ትንሽ እንደ ተራመድኩ እያለ ከፊት ለፊቴ አንዲት ልጅ እግር ኢትዮጵያዊ ብቻዋን እያወራች ስታልፍ ስመለከት በመደናገጥ ሰላምታ አቅረብኩላት፣ መልስ ሳትሰጠኝ አለፈች! ደነገጥኩና ባለሁበት ቆሜ በአይኔ ተከተልኳት … በፈጣን እርምጃ የሚያቃጥል የሚለበልበውን መሬት የምትደቃበትን የጠቆረ ባዶ እግሯን፣ እንደነገሩ ከላይዋ ላይ ደረብ ያደረገችውን ጥቁር “አበያዋን” እና ከፍ ሲል የተንጨፈረረ ጸጉሯን እያየሁ ፈዝዠ ቀረሁ … ከድንጋጤና ከፍርሃት ለአፍታ ነፍሴ መለስ ሲልልኝ ጠደፍ ጠደፍ ብየ ወደ ሔደችበት አቅጣጫ ተከተልኳት … ርቃኛለች … ሮጨ ልደርስባት ባለመቻሌ መኪናየን ወዳቆምኩት በመሔድ አስነስቸ ተከተልኳት … በደቂቃዎች ልዩነት ተሰወረችኝ! ምናልባት በዙሪያው በቆሙት መኪኖች መካከል፣ በመንገዱ ዳርም ሆነ በቤቶች አጥር ጥላ ፈልጋ ደክሟት አረፍ ብላ እንደሆነ በማለት መኪናየን አቆሜ ፍለጋየን ቀጠልኩ … ብዙ ሞክሬ አልተሳካልኝም … ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰላም እያልኳት ገላምጣኝ የሄደቸው እህት የለችም!
በትካዜ ተውጨ በአሳቻ መንገድ አገኛት እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባው እያማተርኩ ሳቀና ከጅዳ ቆንስል ግቢ በግምት 600 መቶ ሜትር ርቀት በአንድ አረብ ቱጃር ቤት አጥር ስር በሚገኝ አንድ ዛፍ ስር፣ ከመንገዱ ዳር አንዲት እህት ወድቃ ተመለከትኩ! ክው ክው ብየ ደነገጥኩ … ተጠጋኋት! የሚያምረው አይኗ ወይቧል፣ ሰውነቷ ደግሞ ዝላለች፣ ላብ ፊቷን አውዝቶታል፣ አፏ ግን አመድ መስሎ ደርቋል! ጠይም ባለ ሰልካካዋ አፍንጫ ለግላጋ መልከ መልካሟን እህት ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ማውራት ቻልኩ … ለነገሩ ማውራት አይባልም! ለረጅም ደቂቃዎች ለማውራት ያደረግኩት ሙከራ በሰጠችኝ ጥቂት መልስ አፏ ተፈታ ማለቱ ይቀላል! ዝርዝር ማውራት ግን አትፈልግም … ምንም አይነት እርዳታ እንደማትፈልግ በአጭሩ ገለጸችልኝ! … በቃ ከዚህ ባለፈ ብዙ ማውራትና መቀጠል አልቻልኩም! የማደርገው ባጣ ቢያንስ በቆንስሉ መጠለያ ግቢ ከታጨቁትና በከፋ አደጋ ላይ እንዳሉ ከሰማሁትና አይቸ ካረጋገጥኩት 150 ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ጋር ቢደባልቋት በሚል ለጅዳው ቆንስል ሃላፊ ለአቶ ዘነበ ከበደና ለዲያስፖራው እና በመጠለያ ላሉት ተፈናቃዮች እህቶች ተጠሪ ዲፕሎማት ለወ/ሮ ሙንትሃ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩላቸው አያነሱም …